|
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት የምታጠናክር መሆኗን
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ |
| አዲስ አበባ መስከረም 24/1999
- ኢትዮጵያ በሶማሊያ የተረጋጋና ምቹ የሆነ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን አሁንም ሆነ ወደፊት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደ ምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ይህን ያስታወቁት በተባበሩት መንግሥታት የሶማሊያ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ኤልፋልን ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡ኢትዮጵያ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት ከተባበሩት መንግሥታት፣ ከኢጋድና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን ይበልጥ አጠናክራ ለመሥራት ዕቅድ እንዳላት አስታውቀዋል፡፡በእነዚህ መድረኮች የሶማሊያ ሰላምን አስመልክቶ የተወሰዱ ውሳኔዎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ መሆን አለባቸው ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምንም መግለጻቸውንም አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በውይይቱ ላይ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እውቅና የሰጠው የሶማሊያ ፌዴራላዊ የሽግግር መንግሥት ተጨባጭ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውም አመልክተዋል፡፡በአሁኑ ወቅትም የኢጋድ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ የሚገባበትን ሁኔታ የመንግሥታቱ ድርጅት በአፋጣኝ ማመቻቸት እንዳለበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ አምባሳደር ፋል በሶማሊያ ባሉ የፀጥታ ችግሮችና ሰላምን ማምጣት በሚቻልበት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር መወያየታቸውን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የተረጋጋ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ቀንድም ሰላም እንዲሰፍን እየተጫወተች ያለው ሚና በጣም የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ ኢዜአ |
|
|
|
|