|
በትግራይ 10ኛ ክፍል ከተፈተኑት ተማሪዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሁለትና ከዛ በላይ ነጥብ አገኙ |
መቀሌ መስከረም 24/1999/ዋኢማ/ በትግራይ ክልል በ1998 ዓ ም የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሁለት ነጥብና ከዛ በላይ ማግኘታቸው ተገለጸ ። የክልሉ ትምህርት ቢሮ የፈተናና ምዘና ክፍል ኃላፊ አቶ ትርፈ ብርሃነ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት ባለፈው የትምህርት ዘመን በ55 መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶች በ10ኛ ክፍል ለፈተና ከቀረቡት 29 ሺ 894 ተማሪዎች ውስጥ 15 ሺ 731 ተማሪዎች ሁለትና ከዛ በላይ ነጥብ አግኝተዋል ። ይኸውም በትምህርት ዘመኑ ለፈተና ከቀረቡት ተማሪዎች ውስጥ 52 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት የተጠቀሰውን የሚያበረታታ ውጤት ማስመዝገባቸውን የክፍል ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል ። በክልሉ በብሄራዊ ፈተናው ሁለትና ከዛ በላይ ነጥብ ካገኙት 15 ሺ 731 ተማሪዎች 4 ሺ 996ቱ ሴት ተማሪዎች ሲሆኑ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎና ውጤታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን እንደሚያሳይ አስረድተዋል ። በክልሉ አሁን የተመዘገበው የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ውጤት በ1997 ዓም ከተመዘገበው ውጤት ጋር ሲነጻጸር በ8 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አቶ ትርፈ ገልጸዋል ። በትግራይ ክልል በ1997 ዓም የትምህርት ዘመን የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከወሰዱት 24 ሺ 20 ተማሪዎች 10 ሺ 561 ተማሪዎች ሁለትና ከዛ በላይ ነጥብ አምጥተው እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል ሲል ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ። |
|
|
|
|