በረሃማነትን ለመቀነስ የተጠናከረ አከባቢን የመከላከል ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ጅጅጋ መስከረም 24/1999/ዋኢማ/ የበረሃማነት መስፋፋት በዝናብ አጠር አከባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዳያደናቅፈው የተጠናከረ አከባቢን የመከላከል ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

በረሃማነትን በመከላከልና በማልማት ተግባር ላይ ያተኮረና ለአራት ቀናት በጅጅጋ ከተማ ሲካሄድ የቆየው አውደ ጥናት ዛሬ ሲጠናቀቅ የድራይ ላንድ ኩኦርድኔሽን ብሄራዊ አስተባባሪ አቶ አብይ አለሙ እንደገለፁት፤ የበረሃማነትን መስፋፋት በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት አደናቃፊ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ድርጅቱ ሆፕ ፎር ዘሆርን ከተባለ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በክልሉ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊና አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሱማሌ ክልል እየተስፋፋ የመጣውን በረሃማነትን ለመከላከል የሚያስችል የድርጊት መርሃ ግብር ለማዘጋጀት አውደ ጥናቱ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

በረሃማነትን ለመከላከል እየተነደፈ ያለው ፕሮጀክት ተግባራዊ ካልሆነ በክልሉ የምግብ ዋስትና ችግር ሊወገድ እንደማይችል አቶ አብይ ገልፀዋል፡፡

ዓውደ ጥናቱ በረሃማነትን በመከላከል ዙሪያ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎችና ከአለም አቀፍ የተገኙ ተግባራዊ የችግር መፍቻ ዘዴዎችን በሱማሌ ክልል ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ፖሊሲዎችንና የድርጊት መርሃ ግብሮች መንደፍ አላማው ማድረጉን አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡

በክልሉ በረሃማነትን መከላከል የሚያስችል ፖሊሲ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት የዝናብ አጠር አካባቢን ልማት በማፋጠን የምግብ ዋስትና ችግርን ለማስወገድ እንደሚረዳ አስታውቀዋል፡፡

ድርጅቱ በረሃማነትን ለመከላከል በመስኩ ጥናት ለሚያካሂዱ ባለሙያዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የበጀት ድጋፍና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ አስተባባሪውን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡