ድርጅቱ ለአማራጭ መሰረታዊ ትምህርት ማጠናከሪያ 195 ሺ ብር የሚያወጡ ቁሳቁስ በዕርዳታ ሰጠ

አሶሳ መስከረም 24/1999/ዋኢማ/ አክሽን ኤድ ኢትዮጵያ የአሶሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለአማራጭ መሰረታዊ ትምህርት ማጠናከሪያ የሚረዱ ግምታቸው 195 ሺ ብር የሆኑ የተለያዩ ቁሳቁስ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ በዕርዳታ ሰጠ።

አክሽን ኤድ ኢትዮጵያን በመወከል ዕርዳታውን ያስረከቡት አቶ ፍሰሀ ከበደ እንደተናገሩት የክልሉ ትምህርት ቢሮ የተለገሱት ስድስት ሞተር ሳይክሎችና አንድ ኮምፒውተር ከነ ፕሪንተሩ በክልሉ አማራጭ መሰረታዊ ትምህርት ለማስፋፋት እየተደረገ ላለው ጥረት ማጠናከሪያ የሚውሉ ናቸው።

ሞተር ሳይክሎቹ አማራጭ ዊ ትምህርት እየተሰጠባቸው ላሉት ለአጋ ሜቲ፣ ያሶ፣ ካማሽ፣ ሲርባባይ፣ ኮሞሻና ኦዳቢልዲ ጊሉ ወረዳዎች የሚከፋፈሉ ሲሆን፤ ኮምፒውተሩ ለቢሮው የተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮን በመወከል ዕርዳታውን የተቀበሉት በቢሮው የትምህርት ፕሮግራምና ሱፐር ቪዝን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሬሳ በበኩላቸው ዕርዳታው ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ጥረት ይደረጋል ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽንማዕከል ዘግቧል።