|
በትግራይ ፈጣን የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት መመቻቸቱ ተገለጸ |
መቀሌ መስከረም 24 /1999/ዋኢማ/ በትግራይ ክልል ለባለሃብቶች ፈጣን የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት በመዘርጋቱ በክልሉ ልማት የሚሳተፉ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሞገስ መስፍን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤በክልሉ ልማት የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ለማበረታታት ለአንድ ባለሃብት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰርቲፍኬት ለመስጠት ሁለት ቀናት ይወስድ የነበረውን ከ50 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ለመስጠት የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል። እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ የመስሪያ ቦታ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች በአንድ ቀን ውስጥ ቦታ የሚያገኙበት መንገድ መመቻቸቱንም ገልጸዋል። ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በክልሉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ የሥራ ሁኔታ በመፈጠሩና የተለያዩ አገልግሎቶች በመሟላታቸው በኢንቨስትመንት መስክ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል። ባለፉት ሦስት ዓመታት ለ268 የልማት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 374 ፕሮጀክቶች ፈቃድ መሰጠቱንም አብራርተዋል። ፕሮጀክቶቹ በኢንዱስትሪ፣በኮንስትራክሽን ፣በአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በቱሪዝም ዘርፍ የሚሠሩ ሲሆኑ፤ ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ከ14 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አስታውቀዋል። በክልሉ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ቁጥር ሊጨምር የቻለው በመቀሌ ከተማ ብቻ የነበረውን የኢንዱስትሪ ዞን ወደ ሌሎች ስምንት ከተሞች በማስፋፋት በኢንዱስትሪ ዞኖቹ የመንገድ ፣መብራት፣ውኃና ስልክ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት በመቻሉ መሆኑን አስረድተዋል። በክልሉ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንጻር አዋጭነት ያላቸው 180 ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶች በአማካሪዎች ተጠንተው ዝርዝራቸው በበራሪ ጽሁፎችና በመጽሄቶች ተዘጋጅቶ ለባለሃብቶች መሰጠቱን ገልጸዋል ። ባለሃብቶች በጥናቱ በመታገዝ መዋዕለ ንዋያቸውን ተጠቃሚ በሚሆኑበት መስክ ላይ ለማዋል የሚያስችላቸውን ግንዛቤ ማግኘታቸውንም አስታውቀዋል። ጽሕፈት ቤታቸው ከልዩ ልዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የክልሉን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ሞገስ፤ባለፉት 10 ዓመታት የልማት ፕሮጀክቶች ቁጥር ወደ 822 የካፒታል መጠናቸው ደግሞ ወደ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ማደጉንም አብራርተዋል። |
|
|
|
|