|
ባለፈው ዓመት ከ15 ሺ በላይ የቤተሰብ መሪ አርሶ አደሮች የተሻለ ለምነት ባላቸው አካባቢዎች መስፈራቸው ተገለጸ |
| አዲስ አበባ መስከረም 24/1999/ዋኢማ/ በሶስት ክልሎች ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው የሰፈራ ፕሮግራም 15 ሺ 546 የቤተሰብ መሪ አርሶአደሮችን የተሻለ ለምነት ወዳላቸው አካባቢዎች ማስፈር መቻሉን በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ቢሮ አስታወቀ። ባለፉት ሶስት ዙሮች ከሰፈሩት 549 ሺ 545 የቤተሰብ መሪ አርሶ አደሮች ውስጥ 132 ሺ 496 የሚሆኑት በምግብ ራሳቸውን እንደቻሉ ተረጋግጧል። በቢሮው የፕሮግራም አዘጋጅና ግምገማ መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ወልደሚካኤል ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በአማራ፣ ደቡብ ህዝቦችና ኦሮሚያ ክልሎች 30 ሺ 908 የቤተሰብ መሪዎችን የተሻለ ለምነት ወዳላቸው አካባቢዎች ለማስፈር በተያዘው ዕቅድ መሰረት 15 ሺ 546ቱን ማስፈር ተችሏል። በአማራ ክልል በተካሄደው የሰፈራ ፕሮግራም በሰሜን ጎንደር ዞን በቋራ፣ ታች አርማጭሆና ጠገዴ ወረዳዎች እንዲሁም በአዊ ዞን ዳንግላ ወረዳ በሚገኙ 12 ነባርና አዳዲስ የሰፈራ ጣቢያዎቸ 8 ሺ 671 የቤተሰብ መሪዎች ከነቤተሰቦቻቸው መስፈራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል። በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደግሞ በስምንት ወረዳዎች በሚገኙ ስምንት ነባርና አዳዲስ ጣቢያዎች 3 ሺ 567 የቤተሰብ ኃላፊዎች እንዲሰፍሩ ተደርጓል። በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ከመሰላና ሀብሮ ወረዳዎቸ የተንቀሳቀሱ 3 ሺ 308 የቤተሰብ መሪ አርሶ አደሮች በቦኬ ቂኒ፣ ዳሮ ለቡና አንጫሮ ወረዳዎች ባሉ አካባቢዎች መስፈራቸውን አስረድተዋል። በሶስቱም ክልሎች ለሚገኙ ሰፋሪ አርሶአደሮች በነፍስ ወከፍ የመኖሪያ ቤት መስሪያና የእርሻ ቦታ የተከፋፈላቸው ሲሆን፤ አምርተው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ የቀለብ፣ የቤት ስውጥ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ አነስተኛ የእርሻ መሳሪያዎችና የልዩ ልዩ ግበቸቶች ድጋፍ እንደተደረገላቸው ኃላፊው ተናግረዋል። ለዘንድሮ እርሻ የሚውሉ የእርሻ በሬዎችና ምርጥ ዘር ግዥ የሚውል 57 ሚሊየን ብር በፌደራል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ቢሮ በኩል ለክልሎቹ መላኩን አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል። ሰፈራው በተካሄደባቸው ጣቢያዎች የትምህርት፣ የውሃ፣ የሰውና የእንስሳት ጤና ተቋማትን ለማስፋፋት ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ከተገኘ ሶስት ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ውስጥ 80 በመቶ ያህሉ ክልሎቹ ስራ ላይ ማዋላቸውን አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል። ባለፉት ሶስት ዙሮች በተካሄዱ የሰፈራ ፕሮግራሞች ከትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ተንቀሳቅሰው ከሰፈሩት 549 ሺ 545 የቤተሰብ መሪ አርሶ አደሮች ውስጥ 132 ሺ 496 የሚሆኑት በምግብ ራሳቸውን መቻላቸውን በባለሙያዎች በተደረገ የመስክ ጉብኝት መረጋገጡን ከአቶ ብርሃኑ ገልጸዋል። |
|
|
|
|