ኮርፖሬሽኑ 18 ከተሞችን የዲጅታል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ

ሐረር መስከረም 24 /1999/ /ዋኢማ/ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ከ65 ነጥብ4 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ 18 ከተሞችን ዘመናዊ የዲጂታል አውቶማቲክ ስልክ ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ።660 የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማህበራት የሽቦ አልባ ስልክ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገለፀ።

በኮርፖሬሽኑ የምስራቅ ሪጅን ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድ አውክ አበዜ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ ከተሞቹ የዲጂታል አውቶማቲክ ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት በተጠናቀቀው ዓመት በከተሞቹ ለሥራው አስፈላጊ የሆነው የማስፋፋትና የኬብል ዝርጋታ ሥራ በመጠናቀቁ ነው።

ከተሞቹን የዲጂታል ስልክ ተጠቃሚ ለማድረግ ኮርፖሬሽኑ ካከናወናቸው የግንባታና የማስፋፋት ሥራዎች መካከልም የማዞሪያ መሳሪያዎች ተከላ፣የመሳሪያ እቃ ግዠ ፣የኔት ዎርክ ማሻሻል፣ኬብል የመዘርጋት ስራ የህንፃ ግንባታና የትራንስሚሽን መሳሪያዎች ተከላ ሥራዎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

በሪጅኑ እስከተያዘው ዓመት መግቢያ ዘመናዊ የዲጂታል አውቶማቲክ ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑ ከተሞች መካከል 14 ቱ በኦሮሚያ አራት ደግሞ በሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኙ የወረዳ ከተሞች መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ በገጠር የቴሌፎን አገልግሎትን ለማዳረስ በጀመረው መርሐ ግብሩ በተጠናቀቀው ዓመት በኦሮሚያ፣በሶማሌ፣በድሬዳዋና በሐረሪ ህዝብ ክልል ውስጥ የሚገኙ 660 የገጠር ቀበሌዎችን የሽቦ አልባ ስልክ ተጠቃሚ ማድረጉን አቶ ወንድ አውክ ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ ከዲጂታል አውቶማቲክ ስልክና ሽቦ አልባ ቴሌፎን በተጨማሪ በሥሩ በሚገኙ 57 ከተሞች ውስጥ በሳንቲም የሚሰሩ የህዝብ ቴሌፎኖችን በመትከል አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ በክልሎቹ በሚገኙ ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች ላካሔደው የግንባታ፣የማስፋፋትና የኬብል የመዘርጋት ስራ 65 ሚሊየን 474 ሺ ብር ወጪ ማድረጉን አስረድተዋል።

እንዲሁም የሞባይል አገልግሎት በተዳረሰባቸው የሪጅኑ ከተሞች ተጨማሪ የማስፋፋት ሥራ በማከናወን ባለፈው ዓመት መጀመሪያ 21 ሺ የነበረውን የሞባይል ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር ወደ 30 ሺ 114 ከፍ ለማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ የግንባታና የስልክ አገልግሎት ማስፋፋት ሥራዎቹን ያከናወነው በአብዛኛው የስልክ አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው የገጠር ከተሞች መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል ሲል ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።