|
የክልሉን ልማት ለማፋጠን የሚያስችል የህዝብ ግንኙነት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተባለ |
ባሕርዳር መስከረም 24/1999/ዋኢማ/ በአማራ ክልል የተጀመረውን ልማት ለማፋጠን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በቂ መረጃ በመስጠት የልማቱ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል የተጀመረው የህዝብ ግነኙነት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለፁ። በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውለደ ኢትዮጵያዊያን ህዝብና መንግሥት ድህነትን ለመቀነስ የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አያሌው ጎበዜ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣በመንግሥት የተከናወኑ የልማት ተግባራት በህብረተሰቡ እንዲታወቁና አርአያ ሆነው እንዲያገለግሉ ለማስቻል እስካሁን የተሠሩ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች ደካማ ናቸው። በተለይ መንግሥት ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ያስመዘገባቸው የልማት እመርታዎች ለህዝቡ በበቂ መረጃ ተደግፈው ባለመቅረባቸው ህብረተሰቡ ስለክልሉ በቂ ግንዛቤ አለው ለማለት እንደማይቻል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል። በቅርቡ የአማራ ክልልና የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ከአካሄዱት ውይይት ለመገንዘብ የተቻለው በአገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ በፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ስለተከናወኑ ተግባራት ነዋሪዎቹ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑን ነው ብለዋል። በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ስለሀገራቸውና ክልላቸው በቂ መረጃ ባለማግኘታቸው በልማቱ መስክ በስፋት እንዳልተሰማሩ መግለፃቸውን የተናገሩት አቶ አያሌው፤በቅርቡ የልዑካን ቡድኑ ከነዋሪዎቹ ጋር ያካሄዷቸው ውይይቶች የተሻለ ግንዛቤን እንዳስጨበጧቸው አብራርተዋል። በሎስአንጀለስ፣ሳኖዜ፣ሲያትል፣አትላንታ፣ኦሃዩ፣ዋሽንግተንና ቦስተን ግዛቶች ለሚኖሩ ወገኖች ስለክልሉና ሀገሪቱ ልማትና እድገት በምስልና ድምጽ የተደገፈ የህዝብ ግንኙነት ሥራ መካሄዱን ገልጸው፤ነዋሪዎቹን ከመንግሥትና ከህዝቡ ጋር ተቀራርበው ለመስራት ያነሳሳቸው መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ የሀገራቸው መንግሥትና ህዝብ ድህነትን ለመቀነስ በሚያደርጉት ዘርፈ ብዙ ትግል ውስጥ በተለያዩ የልማት መስኮች በጋራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን እንደገለፁም አቶ አያሌው አስረድተዋል። እስከዛሬ መንግሥት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ስላሉ የልማት ተግባራት ለምን በቂ መረጃ እንዳልሰጠ የጠየቁት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ የአሁኑ እርምጃ የዘገየ ቢሆንም ወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የመገናኛ መረቦችም እንዲስፋፉ ማሳሰባቸውን ርዕሰመስተዳድሩ ገልፀዋል። የክልሉ መንግሥት ከጉብኝቱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ሌሎችየልማት አጋሮች በቂ መረጃ አለመሰጠቱን በመረዳቱ ወደፊት መረጃዎችን በስፋት ማዳረስ እንዳለበት መገንዘቡን ገልጸዋል። በመሆኑም በክልሉ የተጀመረውን ልማት ለማፋጠን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በኮምፒዩተር የመረጃ መረብ፣በመገናኛ ብዙሀን፣በጽሁፍ መረጃዎች፣በጉብኝታዊ ገለጻዎችና በመሳሰሉት ተግባራት በቂ መረጃ በመስጠት የልማቱ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል የተጀመረው የህዝብ ግነኙነት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|