የአርባ ምንጭ አዞ ዕርባታ ጣቢያ ባለፈው የበጀት ዓመት ከሶስት ሺ በላይ የአዞ ቆዳ ለዓለም ገበያ ማቅረቡን አስታወቀ

አርባ ምንጭ መስከረም 24/1998/ዋኢማ/ የአርባ ምንጭ አዞ ዕርባታ ጣቢያ ባለፈው የበጀት ዓመት ከሶስት ሺ በላይ የአዞ ቆዳ ለዓለም ገበያ ማቅረቡን አስታወቀ። በውጭው ማህበረሰብ ዘንድ በምግብነት ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣውን የአዞ ሥጋ ለገበያ ለማቅረብና የሰጎን ዕርባታ ለመጀመር ማቀዱንም ገልጿል።

የዕርባታ ጣቢያው ኃላፊ አቶ አሠግድ ገብሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ጣቢያው ባሉት ዘጠኝ ሺ አዞዎችን መያዝ የሚችሉ 124 ገንዳዎች አማካይነት እያካሄደ ባለው ዕርባታ ከአዞ ቆዳ ምርት በተጨማሪ ዘመናዊ ቄራ በማደራጀት የአዞ ስጋን አዘጋጅቶ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የአዞ ቆዳ አቅርቦት ጥያቄ ለማሟላትና አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ የምትሆንበትን መንገድ ለማመቻቸት ማዕከሉ በበጀትና በቁሳቁስ መጠናከር እንደሚኖርበት ጠቁመው፤ የዕርባታ ጣቢያው የአዞ ቆዳን መሸጥ ከጀመረበት ካለፉት 11 ዓመታት ወዲህ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ያህል ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

ጣቢያው 3 ሺ 100 አዞዎችን ለመሸጥ ባካሄደው ዓለም አቀፍ ጨረታ ባሌ ኢንተርናሽናል የተባለ የንግድ ተቋም ጨረታውን አሸንፎ በመግዛት ዕርድ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ከሽያጩ ከ150 ሺ ዶላር በላይ ገቢ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ማዕከሉ ከአባያና ጫሞ ሃይቆች እንዲሁም በዙሪያው ከሚገኙ ደሴቶች በዓመት እስከ 12 ሺ የአዞ እንቁላሎችን ሰብስቦ በመፈልፈልና በማርባት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በሃይቆቹ ዙሪያ ባሉ 49 የእንቁላል መጣያ ቦታዎች አማካይነት የተፈለፈሉ ጫጩቶቹን ወደ ማራቢያ ገንዳዎች አዛውሮ በማሳደግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

አንድ የአዞ ጫጩት በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለዕርድ ደርሶ ቆዳውን ለሃገር ውስጥና ለውጪ ገበያ እንደሚቀርብ ኃላፊው ጠቁመዋል።

አዞዎቹ በአካባቢው ባሉት ሃይቆች ውስጥ ለምግብነት የሚጠቀሙበት የአሳ ምርት በመቀነሱ በአካባቢው ዕድሜያቸው የገፉ ፈረሶችና የቀንድ ከብቶችን በመግዛት መኖ እያዘጋጀ መሆኑንም አቶ አሰግድ ገልጸዋል።

የአርባ ምንጭ አዞ ዕርባታ ጣቢያ ከአዞ ዕርባታ ስራ በተጨማሪ የሀገር ውስጥና የውጭ ሃገር ጎብኚዎችን በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው መጠቆማቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።