ኢንስቲትዩቱ ከ5ሺ ለሚበልጡ የስራ አስፈጻሚ አካላትየአቅም ግንባታ ሥልጠና ሊሰጥ ነው

ባህር ዳር መስከረም 24/1999/ዋኢማ/የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በተያዘው የበጀት አመት ከ5 ሺ500 ለሚበልጡ የስራ አስፈጻሚ አካላትን የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አምባው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት በኢንስቲትዩቱ የሚሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለክልል፣ዞንና ለወረዳ እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ የልማት ድርጅቶች ለሚሠሩ የሥራ አስፈጻሚ አካላት ነው።

ሥልጠናዎቹ በመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ጋር የተጣጣሙና ፍላጎትን መሠረት አድርገው የተቀረፁ 19 የትምህርት መስኮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከስልጠናዎቹ መካከልም የስትራቴጅክና ውጤት ተኮር ዕቅድ አዘገጃጀት፣ ዘመናዊና የሪከርድ ስራ አመራር፣ የሰው ኃይል አጠቃቀም፣ የፋይናንስና የፕሮጀክት ሥራ አፈፃፀም እንደሚገኙበት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፆታና ልማት ያላቸውን ትስስር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማሳየት የሚያስችል የሥርዓተ ፆታና ልማት ሥልጠና መቀረፁን ያመለከቱት አቶ ደሳለኝ የጠቅላላ ጥራት ቁጥጥር ስራ አመራር፣ የዕቅድ ምንነትና አዘገጃጀት፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ስልጠናዎችም በስልጠናው እንደሚካተቱ አስታውቀዋል።

ኢንስቲትዩቱ በቅርቡ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ስልጠና ለመስጠት በክልል፣በዞን፣በወረዳና በተለያዩ የልማት ድርጅቶች ባካሄደው ጥናት መሠረት 5 ሺ 507 የስራ አስፈጻሚ አካላት ስልጠናውን ለመውሰድ ፈቃደኝነታቸውን አንዳሳዩ ጠቁመው፣ተጨማሪ ሰልጣኞችን ለመቀበል ኢንስቲትዩቱ ሰፊ ጥናት እያካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።

እስከአሁን ለመሰልጠን ፍላጎታቸውን የገለፁ ሰልጣኞች ቁጥር ከተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ3ሺ 500 ሰልጣኞች ብልጫ እንዳለውና በተያዘው ዓመት ሰፊ የስልጠና አማራጮች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ለሥልጠናው የሚውል 1ሚለየን 752 ሺ ብር ከክልሉ መንግስት መመደቡን አስታውቀዋል።

ስልጠናውን ውጤታማ ለማድረግ በቂ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን መምህራን ለመቅጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀው፣ ተቋሙን በሰው ኃይል የማደራጀት ስራ በሰፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል ሲል ዋልታ ዘግቧል።