|
የውሀ ሀብት ልማት ሚኒስቴር የንጹህ የመጠጥ ውኃና የሳንቴሽን ሽፋንን በሁሉም የገጠር አካባቢዎች ለማዳረስ የሚያስችለው ፕሮግራም ስራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ |
አዲስ አበባ መስከረም 24/1999/ዋኢማ/ የውሀ ሀብት ልማት ሚኒስቴር የንጹህ የመጠጥ ውኃና የሳንቴሽን ሽፋንን በሁሉም የገጠር አካባቢዎች በሰባት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማዳረስ የሚያስችል የዩኒቨርሳል አክሰስ ፕሮግራም መጀመሩን አስታወቀ። ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ ከ10 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ። በሚኒስቴሩ የገጠር መጠጥ ውኃና የሳኒቴሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አብዲ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ፕሮግራሙ የገጠር አካባቢዎች የንፁህ የመጠጥ ውሀና የሳንቴሽን ሽፋንን በማሳደግ የአርሶ አደሩ ምርታማነት የሚሻሻልበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው። በዚህም በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ለገጠሩ ህብረተሰብ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት 98 በመቶ፣ የሳንቴሽን ሽፋን ደግሞ መቶ በመቶ ለማድረስ የሚያስችል መርሃ ግብር ተቀርጾ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ባለፈው ዓመት በተደረገው እንቅስቃሴ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ 35 በመቶ የነበረው የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ወደ 41 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልፀው፤ በሳኒቴሽን በኩልም 17 የነበረው ወደ 20 በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችል አስረድተዋል። የገጠር የመጠጥ ውሀ ሽፋንን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሳደግ ለአዳዲስ ግንባታና ጥገና ከ8 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ ብር፣ ለሳኒቴሽን አገልግሎት ማስፋፊያ ደግሞ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን በላይ ብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ገንዘቡ ከዓለምና የአፍሪካ ልማት ባንኮች፣ ከኔዘርላንድስ መንግስት፣ ከዩኒሴፍና ዩኤንዲፒ እንዲሁም ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንደሚገኝ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ውስጥም ከ992 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ገንዘብ በህብረተሰቡ የጉልበት፣ የማቴሪያልና የገንዘብ አስተዋጽኦ እንደሚሸፈን ገልጸዋል። በነዚህ ዓመታት ውስጥ የ47 ሺ 190 ልዩ ልዩ ነባር የውሃ ተቋማት ጥገና፣ 149 ሺ 24 አዳዲስ ተቋማት ግንባታ እንደሚካሄድም ኃላፊው አመልክተዋል። በተመሳሳይ በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አማካይነት ለገጠሩ ህብረተሰብ በሚሰጠው የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ 13 ሚሊየን 388 ሺ 678 መጸዳጃ ቤቶች እንደሚገነቡ ገልፀዋል። ፕሮግራሙን ለመተግበር የጥናት፣ ዲዛይ፣ ቁጥጥርንና ዓቅም ግንባታ፣ የህብረተሰቡን አስተዋጽኦ ጨምሮ በየዓመቱ 1 ቢሊየን 248 ሚሊየን 555 ሺ 183 ብር ወጪ እንደሚሆን ገልጸው፤ በዚህም 21 ሺ 289 አዳዲስ ተቋማት እንደሚገነቡ ተናግርዋል። ይህንን ግዙፍ ሥራ ለማከናወን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት 49 ሺ 174 ባለሙያዎች አሰልጥኖ መመደብ፣ የወረዳ አስተባባሪዎችና አገልግሎት ሰጪዎችን የማደራጀት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ሥራውን በታሰበው ፍጥነት ለማከናወንም ልዩ ልዩ ኤሌክትሮሜካኒካል፣ ሲቪል ዕቃዎችና ማሺነሪዎች ለመገጣጠም በጅምላ ግዢ ለማቅረብ በፌዴራል መንግስት ደረጃ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኃላፊው አሳስበዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የመጠጥ ውሀና ሳኒቴሽንን ከጤና ጥበቃና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን ገልፀዋል። በመግባቢያ ሰነዱ መሰረት የትምህርት ሚኒስቴር የስነ ንጽህና ትምህርትን በትምህርት ቤቶች የመሰጠት፣ ጤና ጥበቃ ደግሞ ሰርቶ ማሳያዎችን በማዘጋጀት የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግና የሳኒቴሽን መገልገያዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራዎች በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰሩ ኃላፊው አመልክተዋል። ዋኢማ ዓአ/ሙተ |
|
|
|
|