|
በቅጅ መብት ጥሰትና ዘረፋ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለመከላከል የወጣውን ህግ ማስፈጸም እንደሚገባ ተገለፀ |
አዲስ አበባ መስከረም 23/1999/ዋኢማ/ በቅጅ መብት ጥሰትና ዘረፋ ላይ የተሰማሩ ህገ ወጥ አካላትን ህግ ፊት ለማቅረብ የወጣውን ህግ ለመተግበር ህግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው አካል ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባው የኢትዮጵያ የአዕምራዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ገለፀ።. የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ጌትነት ሁነኛው ዛሬ በፍትህ ሚኒስቴር አዳራሽ ለአንድ ቀን በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ተፈፃሚነት ላይ በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ እንደገለፁት፤ ህገ ወጥ የኮፒራይትን ጥሰት በመከላከል ባለመብቶች የድካማቸው ፍሬ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ፖሊስ ፤ ዓቃቢ ህግና ፍርድ ቤቶች የወጣውን ህግ በአግባቡ ሊተገብሩትና ሊያስፈጽሙት እንደሚገባ አስረድተዋል። በ1995 ዓ.ም የተቋቋመው የአዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በአገሪቱ የሚታየውን የቅጅ መብት ጥሰት ለመከላከልና አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ ከባለመብቶችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የክልል መንግስታት የክልል አዕምሯዊ ንብረት ምክር ቤቶችንና አግባብ ያላቸው ተቋማትን ለመመስረት የጀመሩት እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት እያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ አሰፋ ከሲቶ በበኩላቸው መንግስት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር በህገ ወጥ ቅጅና ዘረፋ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለመከላከል መጠነ ሰፊ ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ ማድረጉን ገልፀው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ ጥረቱን እንደሚቀጥል አስረድተዋል። የቅጅ መብትና የተዛማጅ መብቶችን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት፣ በመስኩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሥራዎቻቸውን የሚገመግሙበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበትና ጉድለቶቻቸውን የሚያስተካክሉበት የጋራ መድረክ ሊኖራቸው እንደሚገባ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። በተለይ በቅርቡ በኪነ ጥበብና ስነ ጽሁፍ መስኮች የተሰባሰቡ የሙያ ማህበራት፣ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮፒራይት የጋራ አስተዳደር ማህበር ማቋቋማቸው ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ በአውደ ጥናቱ አቃቢያነ ህግ፣ የፖሊስ አካላት፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና አሣታሚዎች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|