ተቋሙ 93 በምርምር የተሻሻሉ የሰብል፣ የመኖ፣ የጓሮ አትክልትና የፍራፍሬ ዝሪያዎችን ሰበሰበ

ጅጅጋ መስከረም 23/1999/ዋኢማ/ የሶማሌ ክልል አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ምርምር ተቋም 93 የተሻሻሉ የሰብል፣ የመኖ፣ የጓሮ አትክልትና የፍራፍሬ ዝሪያዎችን ከአከባቢው የአየር ፀባይ ጋር ለማላመድ ከውጭና ከአገር ውስጥ የምርምር ማዕከላት መሰብሰቡን ገለፀ፤ ለቀጣይ የምርምር ስራዎች መሠረት የሚጥሉ 18 የቅኝት ጥናቶች የሚካሄዱ መሆናቸውንም አስታወቋል።

የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሀዲ ኢጌ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት ከኡጋንዳ፣ ከዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከመልካሳና መልካ ወረር የምርምር ማዕከላት የተሰበሰቡት በምርምር የተሻሻሉ የሩዝና የሰሊጥ፣ የእንስሳት መኖ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ሙዝና ፓፓዬ ዝርያዎች ናቸው።

በጅጅጋ፣ ጎዴና ቀላፎ አከባቢዎች ከተያዘው ዓመት ጀምሮ በዝናብና በመስኖ ውሃ እንዲላመዱ የሚደረጉት እነዚሁ ዝርያዎች ምርታማነትን የሚገድቡ ክስተቶችን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡት እስከ ሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተመርጠው ለተጠቃሚዎች የሚቀርቡ መሆናቸውንም ምክትል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

በተለይ ከኡጋንዳ ከመጡት 31 የሩዝ ዝሪያዎች መካከል በመስኖ በሚለሙ የክልሉ አከባቢዎች የአፈር ጨዋማነትን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡትን ለመለየት የማላመዱ ስራ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ በዚህ ዓመት ወደፊት ለሚካሄዱ ሌሎች የምርምር ስራዎች መሠረት የሚጥሉና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ለመለየት የሚያስችሉ 18 የቅኝት ጥናቶችንም ለማካሄድ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ መሀዲ ገልፀዋል።

የቅኝት ጥናቶቹ በእንስሳት በሽታ፣ በግጦሽ መሬት አያያዝ፣ በአፈር ለምነትና ማዳበሪያ አጠቃቀም፣ በሰብል ምርቶች፣ በመድኃኒት እፅዋትና በተፈጥሮ ሃብት ገፅታ ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በፋፋን ከተማ እየተካሄደ ያለውን የተቀናጀ የእንስሳት እርባታና ምርምርን ጨምሮ ለዝርያ ማላመድ፣ ለቅኝት ጥናቶችና ለአቅም ግንባታ ስራዎች የክልሉ መንግስት ዘንድሮ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መመደቡንም ምክትል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።