አርቲሚዝያ የተባለ ለመድሃኒትነት የሚያገለግል ተክል በመቀሌ በችግኝ ማፊያዎች እየተሞከረ መሆኑ ተገለፀ

መቀሌ መስከረም 23/1999/ዋኢማ/ በመድሃኒት ፋብሪካዎች ለመድሃኒትነት ቅመማ የሚያገለግል አርቲሚዚያ የተባለ ተክል በመቀሌ አከባቢ በሚገኙ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች እየተሞከረ መሆኑን የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ዘርፍ የደንና አግሮፎረስትሪ ቡዱን መሪ አቶ ጸጋዘአብ ተካ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት የተክሉ ቅጠል በፋብሪካዎች ተጨምቆ አርቲሚዚን የተባለ መድሃኒት እንደሚወጣውና ለወባ፣ለካንሰርና ለተለያዩ በሽታዎች በመድሃኒትነት እንደሚውል አስታውቀዋል ።

ይኸው ተክል ባሳለፍነው ጳጉሜን 1998 በመቀሌ ኩሓ አከባቢ በሚገኙ ሁለት የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች ፍሬው ተዘርቶ በቁጥር 5 ሺ ያህል መብቀላቸውን ገልጸዋል ።

ቢሮው አሁን ዘር የማባዛት ሥራ ብቻ እየሰራ በመሆኑ ፍሬውን እንጂ ለመድሃኒትነት የሚያገለግለውን ቅጠሉን ለጊዜው አይጠቀምበትም ያሉት አቶ ጸጋአብ በቀጣዩ ግን ጥናት በማካሄድ በዝናብና በዘመናዊ መስኖ በመታገዝ በስፋት እንዲመረት ዕቅድ መኖሩን አስረድተዋል።

ለአገራችን መድሃኒት ፋብሪካዎችና ለሌሎች አገሮች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊያሰገኝ የሚችለው የአርቲሚዚያ ተክል ቆላማ የአየር ጸባይ እንደሚስማማውና አሰከ ሶስት ሜትር ርዝማኔ የሚኖረው ሲሆን በስድስት ወራት ምርቱ ተሰብስቦ ለአገልግሎት እንደሚውልም አብራርተዋል ።

በአፍሪካ እንደ ኬንያ፣ታንዛኒያና የመሳሰሉት አገሮች እንደሚመረትና ለወደፊቱም በክልሉ በአርሶ አደር ደረጃ ለማምረትና በስፋት ተጠቃሚ ለማድረግ ምርቱ ተሰብስቦ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ እንደሚወሰን ጠቁመዋል ።

አርቲሚዚያ በኤስያ በተለይም በቻይና እንደማንኛውም ሰብል በእርሻ ማሣዎች ተዘርቶ ምርቱ ተሰብስቦ ለፋብሪካዎች እንደሚቀርብና አስካሁን ባለው መረጃም በዓለም ደረጃ 4 ቢልየን ዶዝ ብቻ የሚቀርብ ቢሆንም ፋብሪካዎች ምርቱ በአስር እጥፍ እንዲቀርብላቸው ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል ።

በተመሣሣይም ቢሮው ከደቡብ ክልል ያስመጣውን 184 ሺ 809 የእንጆሪ ተክል ቁርጥራጮች በመቀሌ ከተማ ዒላላ በተባለ የችግኝ ማፊያ ጣቢያ እያበዛ መሆኑን አቶ ጸጋአብ ተካ ገልጸዋል ።

ለሃር ትል በምግብነት የሚያገለግለው የእንጆሪ ተክል ካሳለፍነው ዓመት መጨረሻ አከባቢ ጀምሮ ሙከራው በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ በመሆኑ በቀጣዩ ዕቅዳቸው በገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት ለአርሶ አደሩ ትምህርት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል ።

የሃር ምርት በውጭም በአገር ውስጥም እጅግ ተፈላጊ ነው ያሉት አቶ ጸጋአብ በክልሉ ከሚገኙ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ጣቢያዎች የሚወጡ ወጣት አርሶ አደሮች ሥራ ፈጣሪ ሆነው ኑሮአቸውን ለመለወጥ እንዲችሉ የሙያ ድጋፍ እየተደረገላቸው በስፋት እንዲያመርቱ እንሚደረግም አስረድተዋል ።

የኢንጆሪ ቅጠል የሚመገቡ የሃር ትሎች በመቀሌ ከተማ በሚገኝ ሌላ የሙከራ ጣቢያ የሚያበረታታ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የቡዱን መሪው አመልክተዋል ሲል ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።