ዩኒቨርስቲው የስኳር ድንችን ቅጠል ጠቀሜታ ለአርሶ አደሮች በማስተዋወቅ ላይ መሆኑን ገለፀ

ሐረር መስከረም 23/ 1999/ ዋኢማ/ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ስኳር ድንች ከሥሩ ይልቅ ቅጠሉ ከፍተኛ የምግብ ጠቀሜታ እንዳለው በመረጋገጡ ለአርሶ አደሮች በማስተዋወቅ ላይ መሆኑን አስታወቀ።በተያዘው የፈረንጆች ዓመት በምርምር ያገኘውን አዲስ የቦሎቄ ዝርያ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት በማባዛት ላይ መሆኑንም ገለፀ።

የዩኒቨርስቲው የምርምርና ስርጸት ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ተፈራ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ የስኳር ድንች ቅጠል ከስሩ የበለጠ በፕሮቲን፣ ቪታሚን ኤ እና በሌሎችም የንጥረ ነገር ይዘቱ በጣም የተሻለ መሆኑ ተረጋግጧል።

እንዲሁም በተክል ውስጥ የማይገኝና በሥጋ፣ በእንቁላልና በወተት ውስጥ ብቻ የሚገኝ ላይሲን የተባለ አሚኖ አሲድ በስኳር ድንች ቅጠል ውስጥ እንደሚገኝ በጥናት መረጋገጡን ዶክተር ታደለ ገልፀዋል።

የስኳር ድንች ቅጠል በእስያና በአንዳንድ የምዕራበ አፍሪካ አገሮች ከፍተኛ ተወዳጅ ምግብ እየሆነ መምጣቱን የጠቆሙት ዶክተር ታደለ፤ በሀገሪቱ ለምግብነት እንዲውል ዩኒቨርስቲው ለአርሶ አደሮች በሰርቶ ማሳያ ላይ ልምድ እንዲወስዱ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ዩኒቨርስቲው በተያዘው የፈረንጆች ዓመት በምርምር ያገኘውን አዲስ የቦሎቄ ዝርያ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት በማባዛት ላይ መሆኑን የምርምርና ስርጸት ዳይሬክተሩ ዶክተር ታደለ ተፈራ ገልፀዋል።

በዩኒቨርስቲው ሠርቶ ማሳያ የምርምር ጣቢያ በመባዛት ላይ የሚገኘውና በዩኒቨርስቲው ተመራማሪዎች በምርምር የተገኘው አዲስ የቦሎቄ ዝርያ የደጋና ወይና ደጋ አካባቢዎች እንደሚስማማ ተናግረዋል።

የቦሎቄ ዝርያው በአርሶ አደሩ እጅ ከሚገኘው የቦሎቄ ዝርያ ከዕጥፍ በላይ ምርት የሚሰጥ፣ በሽታንና ድርቅን የመቋቋም አቅም ያለው ሲሆን ሐረማያ የሚል መጠሪያ እንደወጣለት ዶክተር ታደለ ገልጸዋል።

ዝርያው ከ90 እስከ 100 ባሉት ቀናት ውስጥ ለምርት የሚደርስ ሲሆን በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ተሞክሮ በሄክታር ከ20 አስከ 30 ኩንታል ምርት በመስጠት በአርሶ አደሩ ማሳ ከሚመረቱ ሌሎች የቦሎቄ ዝርያዎች የተሻለና ከፍተኛ ምርት የመስጠት አቅም እንዳለው በምርምር መረጋገጡን አስረድተዋለ።

በብሔራዊ ዘር አጽዳቂ ኮሚቴ የተመሰከረለት ይሄው የቦሎቄ ዝርያ በዩኒቨርስቲው የተለያዩ የምርምር ጣቢያዎችና በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ከሶስት ዓመታት በላይ ምርምር የተደረገበት መሆኑንም ዶክተር ታደለ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርስቲው ባለፉት ሶስት ዓመታት ባደረገው ምርምር በአርሶ አደሩ ተፈላጊ የሆኑ ጨርጨር፣አየነውና ጎፍታ የተባሉ የቦሎቄ ዝርያዎችን በምርምር አግኝቶ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱን ከዳይሬክተሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።