በባህርዳር የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለማቃለል ለ3 ሺ 200 ነዋሪዎች የቤት መሥሪያ ቦታ ይሰጣል

ባሕር ዳር መስከረም 23/1999/ዋኢማ/ በባሕር ዳር ከተማ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል በተያዘው የበጀት ዓመት ከ3 ሺ 200 ለሚበልጡ የከተማዋ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ እንደሚሰጥ የከተማዋ ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ገለፀ።የመኖሪያ ቦታዎችን በማስረከቡ ሂደት ከመሬታቸው ለሚፈናቀሉ አርሶ አደሮችና ባለይዞታዎች ከ47 ሚሊየን ብር በላይ የካሣ ክፍያ መዘጋጀቱንም አስታውቋል።

በጽሕፈት ቤቱ የማስታወቂያ ቡድን መሪ አቶ ስዩም አድማሱ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በባሕር ዳር ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት አስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

በመሆኑም በተያዘው የበጀት ዓመት በተለይ በአነስተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ባለቤት ለማድርግ 1 ሺ 500 የቤተሰብ ኃላፊዎችን ማስተናገድ የሚችሉ የጋራ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል።

በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ለጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውሉ ቦታዎችን የመለየት ሥራ መከናወኑን ያመለከቱት አቶ ስዩም፤በቴክኒክና ሙያ በተለያዩ መስኮች የሰለጠኑ ወጣቶችም በስፋት በግንባታው ሥራ እንዲሳተፉ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ በከተማዋ በመንግሥት ወጭ ከሚገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤት ህንፃዎች በተጨማሪ በማህበር ለተደራጁ፣በግል ለሚሰሩና ምትክ ቦታ ለሚያስፈልጋቸው 1 ሺ 500 ነዋሪዎች አስተዳደሩ ቦታ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

እንዲሁም መንግሥት በሚገነባው የጋራ መኖሪያ ቤት የተወሰነላቸውን ክፍያ ለመክፈል እንዲሁም በግል የመኖሪያ ቤት መገንባት ለማይችሉና ቤታቸው ለሚፈርስባቸው 270 ለሚሆኑ ነዋሪዎችም የከተማው አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በራሱ ወጭ የቀበሌ ቁጠባ ቤቶችን በመገንባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የመኖሪያ ቤቶችን ገንብተው ለመሸጥና ለማከራየት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች በቂ ቦታ መዘጋጀቱን አቶ ሥዩም አመልክተዋል።

በከተዋ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን የጠቆሙት ቡድን መሪው፤ ከመሬት ይዞታ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንዲቻልም የክልሉ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ከአስተዳደሩ አቅም በላይ ሆኖ የቆየውን የካሳ ክፍያ በመረዳትና ከቦታቸው የሚነሱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአግባቡ ለማስተናገድ የክልሉ መንግሥት ከ47 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አቶ ሥዩምን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።