|
በደቡብ ክልል የመስኖ ተጠቃሚዎችን ቁጥር 80ሺ ለማድረስ የሚያስችል እንቅስቃሴ ተጀመረ- |
አዋሳ መስከረም 23/1999/ዋኢማ/ በደቡብ ክልል በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት የመስኖ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ42 ሺ ወደ 80 ሺ ለማሳደግ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ውሃ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፤ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ የ78 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቧል። በቢሮው የመስኖ ልማት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ምትኩ በድሩ ትናንት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ባለው በዚሁ ፕሮግራም በክልሉ 13 ዞኖችና 8 ልዩ ወረዳዎች የ58 የተለያዩ የመስኖ ፕሮጄክቶች አዲስ ግንባታና የ12 ነባር ፕሮጄክቶች የማስፋፍያ ሥራ ይካሄዳል። ከፕሮጄክቶቹ መካከል 33ቱ ዝናብ አጠር በሆኑ የክልሉ ቆላማ አከባቢዎች የሚገነቡና በንፋስ ኃይል የሚሠሩ የከርሠ-ምድር ውሃ መሳቢያ ሞተሮችን በመግጠም ከሰውና እንስሳት መጠቀሚያነት አልፈው ለመስኖ ልማት የሚውሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራ እንደሆነም ተናግረዋል። እንዲሁም 11 ፕሮጄክቶች የጎርፍ ውሃን ቀልብሶ ወደ ማሳ የማስገባት ሥራዎች የሚከናወኑ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ግንባታዎች ክረምት ከበጋ ክልሉን አቋርጠው የሚፈሱ ወንዞችን በስበት ኃይል በመጥለፍ ለመስኖ ልማት እንዲውሉ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል። ለፕሮጄክቶቹ ማስፈፀሚያ የ78 ሚሊየን ብር በጀት ከመንግሥት፤ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከፈረንሳይ የልማት ተራዶኦ ድርጅት(AFD) መመደቡን ሃላፊው ገልፀዋል። ከተመደበው በጀት ውስጥ 90 በመቶው ለግንባታ፤ቀሪው የህብረተሰቡን የመስኖ አጠቃቀም ባህል ለማጎልበት የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ይውላል። ግንባታዎቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ከ38ሺ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ለማልማት እንደሚያስችሉና በዚህም በክልሉ በአሁኑ ወቅት በመልማት ላይ የሚገኘውን 42 ሺ ሄክታር የመስኖ እርሻ ወደ 80 ሺ በማሳደግ የተጠቃሚዎችንም ቁጥር በእጥፍ እንደሚጨምሩ ገልፀዋል። በተለይም ዝናብ አጠር በሆኑ የክልሉ አርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደር አከባቢዎች የፈረንሳይ የመስኖ ልማት ከፍተኛ ባለሙያዎች በግንባታዎቹ ሂደት ከሚሠጡት የቴክኒክ ዕገዛ ባሻገር ህብረተሰቡን ከዘመናዊ የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ ጋር ለማስተዋወቅ የሚያሰችሉ ትምህርቶችን እንደሚሰጡ አስረድተዋል። በደቡብ ክልል ከ450 ሺ ሄክታር በላይ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት ቢኖርም እስከ አሁን ጥቅም ላይ የዋለው ሰባት በመቶው ብቻ እንደሆነ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። |
|
|
|
|