|
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለማጠመናከር 10 ሚሊየን ብር ተመደበ |
አሶሳ መስከረም 23/1999/በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተቋቋሙ 60 የገጠር አነስተኛ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ሕብረት ስራ ማህበራትን ለማጠናከር 10 ሚሊየን ብር መመደቡን የክልሉ የገጠር አነስተኛ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ማስፋፊያ ፕሮግራም አስታወቀ፡፡ የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ክንዴ ተሾመ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት ከተመደበው በጀት ዘጠኝ ሚሊየን ብር ማህበራቱን በቁሳቁስ ለማሟላት፣ የአባላቱንና የሰራተኛውን አቅም ለማጐልበትና ለተሽከርካሪ ግዢ የሚውል ሲሆን ቀሪው 1 ሚሊየን ብር ደግሞ ለባለሙያዎችና ሰራተኞች የሚከፈል ነው፡፡ በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገ እንቅስቃሴ 60 የገጠር አነስተኛ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ሕብረት ስራ ማህበራት በመቋቋማቸው፣በገጠር የሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል የቁጠባ ባህሉን ማሳደግ እንዲችል አስችሏል ብለዋል። የአገሪቱ ግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ የሕብረት ስራ ማህበራትን ማጠናከር መሆኑን ጠቅሰው፣ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና በገጠር የፋይናንስ ስርዓትን ለመዘርጋትና ወደ ገጠር ባንክነት ለማሳደግ የማህበራቱ መቋቋም ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ማህበራቱ 1ሺ 500 አባላት እንዳሏቸው የገለፁት አቶ ክንዴ 171 ሺ 851 ብር ካፒታል ማሰባሰባቸውንም ተናግረዋል፡፡ የማኅበራቱን አባላት ቁጥር በመጪዎቹ አምስት 21ሺ 300 ለማድረስ፣የካፒታል መጠናቸውን ደግሞ ወደ 23 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በማድረስ 50 ሺ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል። |
|
|
|
|