የአረጋውያንን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ የአፈጻጸም መመሪያዎች እንደሚወጡ ተገለጸ

አዲስ አበባ መስከረም 23/1999 ዋኢማ / በተያዘው የበጀት ዓመት የአረጋውያንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል የተነደፈውን ብሄራዊ የድርጊት መርሃግብር ስራ ላይ ለማዋል የአፈጻጸም መመሪያዎች እንደሚወጡና የአስፈጻሚ አካላት እንደሚቋቋሙ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የአረጋውያን ጉዳይ ቡድን መሪ አቶ አሰፋ ባልሄር ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ የአረጋውያንን ማህበራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የሚሰጡ የማህበራዊ አገልግሎቶች ጥራታቸውና ደረጃቸው እንዲጠበቅ፣እንዲሁም ዘላቂና ልማታዊ አቅጣጫን የተከተሉ ለማድረግ ለሚቀጥሉት አስር አመታት እንዲያገለግል የተዘጋጀው የአረጋውያን ብሄራዊ የድርጊት መርሃግብር ስራ ላይ የማዋል እንቅስቃሴ ይከናወናል።

የድርጊት መርሃግብሩ የአረጋውያንን ተሳትፎ ፣ሰብዓዊ መብቶችና መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚያመላክቱ የትኩረት አቅጣጫዎችና 13 ርዕሰ ጉዳዮች የተካተቱበት መሆኑን አቶ አሰፋ ጠቁመው፤በተያዘው የበጀት አመትም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የአፈጻጸም መመሪያዎች፤ እንዲሁም በማዕከልና በክልል ደረጃ የአስፈጻሚ አካላትን የማቋቋም ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡

መርሃግብሩን በስፋት ለማስተዋወቅ በአምስት ክልሎች ትላልቅ አውደ ጥናቶችን ለማካሄድና የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለማከናወን መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው አመት የአረጋውያኑን ማህበራዊ ደህንነት ለመጠበቅ የሚቻልበትን መንገድ ለመፈለግ በልመና ተግባር በተሰማሩ 250 አረጋውያን ላይ ጥናት መደረጉን የገለጹት ቡድን መሪው፤ በጥናቱ ውጤት መሰረት የአረጋውያንን የማህበራዊ ደህንነት ፈንድ ለማቋቋም የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

ለአረጋውያን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ለመስጠትና ሞዴል የአረጋውያን ማዕከል ህንጻ ለመገንባት ከሊዝ ነጻ የሆነ አምስት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የመሰረት ድንጋይ መጣሉን ጠቁመው፤ለግንባታ የሚሆን የገቢማሰባሰቢያ ስራዎች እንደሚከናወኑም አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በማዕከላዊ ስታስቲክስ በተደረገ ጥናት በአገሪቱ ዕድሜያቸው 60ና ከዚያ በላይ የሆነ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን አረጋውያን እንደሚገኙ የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘገባ ያመለክታል።