|
የኦሞ ብሄራዊ ፓርክን ለማደራጀት ከ1 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ ተመደበ |
| አርባ ምንጭ መስከረም 23/1999/ዋኢማ/ በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘውን የኦሞ ብሄራዊ ፓርክ በአዲስ መልክ ለማደራጀትና ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ አፍሪካን ፓርክስ የተባለው ተቋም ከአንድ ሚሊየን ዶላር በሚበልጥ ወጪ የማደራጀት ስራዎችን እያካሄደ መሆኑን ገለፀ።
በአፍሪካን ፓርክስ የኦሞ ብሄራዊ ፓርክ አስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ታዬ ትናንት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ጎብኚዎች የተሟላ ግልጋሎት ማግኘት እንዲችሉ በብሄራዊ ፓርኩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የመገናኛ መሳሪያዎችና የተለያዩ ማዕከላት እየተገነቡና እየተደራጁ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግስት ከቀረጥ ነፃ የሆኑ ዕቃዎች እንዲገቡ መፍቀዱ ጠቅሞናል ያሉት አቶ ሳሙኤል ከዚህ ቀደም በኦሞ ወንዝ ላይ ለሚደረጉ የቱሪስቶች እንቅስቃሴ ፓርኩ አንድ የሞተር ጀልባ ብቻ ስለነበረው አደረጃጀቱን ለማሻሻልና የዱር እንስሳቱን ከህገ ወጥ አደን ለመጠበቅ ከአንድ ሚሊየን ዶላር በሚበልጥ ወጪ የተጀመረው እንቅስቃሴ ውጤት እየታየበት መሆኑን አስረድተዋል።
ለመድሃኒትነትና ቆዳን ለማስዋብ በሚሉ ልማዶች በፓርኩ የሜዳ አህዮችና የአነር ዝርያዎች ላይ ህገ ወጥ አደን እንደሚካሄድ መረጃ መኖሩን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለማስቀረት ለአካባቢው ነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም አስታውቀዋል።
አፍሪካን ፓርክስ ከ64 ሺ ሄክታር መሬት በላይ ስፋትያለውን የኦሞ ብሄራዊ ፓርክ ካለፈው ጥር ጀምሮ ከመንግስት የተረከበ ሲሆን፤ በቱሪስት መስህብነታቸው የሚታወቁ ብዛት ያላቸው ዝሆኖች፣ ጎሾች፣ ድፋርሳዎችና ቀጭኔዎች እንደሚገኙበት ከኃላፊው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል። |
|
|
|
|