በክልሉ 24 ሺ 591 ሕፃናት የአራጭ መሰረታዊ ትምህርት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገለጸ

አሶሳ መስከረም 22/1999/ዋኢማ/ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ24 ሺ 500 በላይ ሕፃናት የአማራጭ መሰረታዊ ትምህርት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የትምህርት ፕሮግራሞችና ሱፐርቪዥን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሬሳ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በትምህርት ዘመኑ 24 ሺ 591 ሕፃናት በክልሉ በተከፈቱ 236 የአማራጭ መሰረታዊ ትምህርት መስጫ ጣቢያዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋል።

ለትምህርት መስጫ ጣቢያዎቹ 500 አመቻች መምህራን መመደባቸውን የገለፁት አቶ ሙሉጌታ፤ ለ1999 የትምህርት ዘመን 60 ተጨማሪ የትምህርት መስጫ ጣቢያዎች መገንባታቸውን አስታውቀዋል።

አመቻች መምህራኑ ቀደም ሲል 10ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ እንደነበሩና ከ1998 ክረምት ጀምሮ የትምህርቱን ጥራት ለመጠበቅ 224 መምህራን በግልገል በለስ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርነት እንዲሰለጥኑ መደረጉን አስረድተዋል።

ለቁሳቁስ ማሟያና ለተጨማሪ ትምህርት መስጫ ጣቢያዎች ግንባታ አራት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የ134 ሺ 400 ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ሙሉጌታን ገልጸዋል።

በክልሉ በ1998 የትምህርት ዘመን 14 ሺ 500 ህጻናት በ176 የትምህርት መስጫ ጣቢያዎች ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ከመምሪያው ኃላፊ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።