በክልሉ ዘጠኝ ሺ ለሚጠጉ የመንግስት ሰራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጠ

ባሕር ዳር መስከረም 23/1999/ዋኢማ/ በአማራ ክልል በወረዳዎች የሚታየውን የማስፈጸም ዓቅም ችግር ለማስወገድ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ዘጠኝ ሺ ለሚጠጉ የመንግስት ሰራተኞች ሥልጠና መሰጠቱን የክልሉ ዓቅም ግንባታ ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት መኮንን አቶ ውድነህ ገዛህኝ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በ114 ወረዳዎች የሚገኙ 8 ሺ 642 የወረዳ የስራ አስፈጻሚዎች ስልጠናው የተሰጠው በክልሉ እየተካሄደ ያለውን የልማትና መልካም አስተዳደር እንቅስቃሴ አቀናጅተው ለመምራት የሚያስችላቸውን የአቅም ለመፍጠር ነው።

አስፈፃሚ አካላቱ በዋናነት መንግስት የገጠርና ከተማ ልማቱን ያፋጥናሉ ብሎ ባስቀመጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጀዎች ላይ ያተኮረ የአጭርና መካከለኛ ጊዜ ሥልጠና የተሰጣቸው መሆኑን አቶ ውድነህ አመልክተዋል።

የስልጠናው መሰጠት በተለይ በክልሉ አንዳንድ ወረዳዎች ጎልቶ ይታይ የነበረውን የዕቅድና የሪፖርት አደረጃጀት፣ አያያዝ፣ አላላክ፣ ወቅታዊነት፣ጥራትና የመሳሰሉት ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚረዳም የህዝብ ግንኙነት መኮንኑ ገልፀዋል።

የክልሉ መንግሥት ካስቀመጠው ፖሊሲና ስትራቴጂ አኳያ በተለያዩ ወረዳዎች ለሚገኙ አስፈፃሚ አካላት የተሰጠው ስልጠና ሥራዎቻቸውንና የዕቅድ አፈፃፀማቸውን በቅደም ተከተልና በጥራት እየመዘኑ በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት አጋዥ እንደሚሆናቸው አቶ ውድነህ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ተግባራዊ የሆነው ያልተማከለ አደረጃጀት ወረዳዎች በበጀት ዓመቱ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ዕቅድ ራሳቸው እንዲያቀርቡ የሚፈቅድ በመሆኑ ዕቅዶቹን ሳይንሳዊ መንገድን ተከትለው እንዲነደፉና እንዲተገበሩ የሚያስችል ዓቅም እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

እንዲሁም አስፈፃሚ አካላቱ በየጊዜው በዕቅድ ክለሳ ምክንያት የሚያጠፉትን የጊዜና የሀብት ብክነት እንደሚያሰቀርላቸውም የሕዝብ ግነኙነት መኮንኑ አስረድተዋል።

በክልሉ የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት የተጠናከረ፣ወቅታዊና ደረጃውን የጠበቀ የዕቅድ አፈፃፀም ክህሎት ኖሯቸው አስተማማኝ የዕቅድ አዘገጃጀት፣ ክትትልና ግምገማ ሥርዓት በመዘርጋት ለክልሉ ልማት መፋጠን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።