|
የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ማዳረስ ትኩረት የተሰጠው ተግባር መሆኑ ተገለጸ |
አዋሳ መስከረም 22/1999/ዋኢማ/ ለ3ኛው ዙር የጤናው ዘርፍ የልማት መርሃ ግብር ስኬታማነት መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በህብረተሰብ ተሳትፎ በሁሉም ቀበሌዎች ማዳረስ ልዩ ትኩረት የተሠጠው መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስትሩ ዶክቴር ቴዎድሮስ አድሃኖም ዛሬ በአዋሳ ከተማ በተጀመረው 3ኛ ዙር የጤና ዘርፍ የልማት መርሃ ግብር ዓመታዊ ግምግማ ላይ እንዳስታወቁት፤ከ1998 ዓም ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች እስከ 2002 ድረስ ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮግራም የሀገሪቱን የጤና ሽፋን በ22 በመቶ ሊያሳድገው ይችላል። ፕሮግራሙ ለእናቶችና ሕፃናት የጤና አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ ያስችላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በወባ በሽታ ምክንያት የሚከሰተውን ሞትና ሕመም ከ22 በመቶ ወደ 10 በመቶ ለመቀነስ እንዲሁም የኤችአይቪ/ ኤድስና ሳንባ ነቀርሳ በሽታዎችን ሥርጭት በሶስት በመቶ ለመቀነስ መታቀዱን ተናግረዋል። የተፋጠነ የመረጃ አላላክና አሰባሰብ ሥርዓት ለመዘርጋት ከጤና ኬላ እስከ ሆስፒታል ያሉት የጤና ተቋማት ከየክልሎቻቸውና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር የሚገናኙበት የኮምፒዩተር መረጃ መረብ የመዘርጋት ሥራ መጀመሩንም አስረድተዋል። ፕሮግራሙን ለማስፈፀም የ37 ቢሊየን ብር በጀት እንደሚያስፈልግና 17 ቢሊየን ብር በመንግሥት የሚሸፈን መሆኑን የተናገሩት ሚኒስቴሩ፤ቀሪው ተግባር በህብረተሰቡ ተሳትፎና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል። የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፍራው ሽጉጤ በበኩላቸው መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን በቤተሰብ ደረጃ ለማዳረስ መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት የክልሉ የጤና ሽፋን ከ10 ዓመታት በፊት ከነበረበት 28 በመቶ ወደ 73 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ለማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። በአብዛኛዎቹ የክልሉ የገጠር ቀበሌዎች በሕዝቡ ተሳትፎ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተግባራዊ በመደረጉ በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ በመመዝገብ ላይ ቢሆንም፤በአንዳንድ አካባቢዎች በግልና አካባቢ ንጽህና ጉድለት እንዲሁም ባልተመጣጠነ አመጋገብ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለማቃለል በመንግሥት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል። ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ቀናት በሚቆየው የመርሃ ግብር አፈጻጸም ግምገማ 312 የሚሆኑ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የጤና ቢሮ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች፣የተለያዩ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶችና መንግሥታዊ ድርጅቶች ተወካዮች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|