|
ድርጅቱ በ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ የ13 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በወቅቱ ለማጠናቀቅ ክትትል እያደረገ ነው |
| አዲስ አበባ መስከረም 22/1999/ዋኢማ /መንግስት በ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ያስጀመራቸውን የ13 ዩኒቨርስቲዎች ግንባታ በወቅቱ ለማጠናቀቅ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ መሆኑን የጀርመን ቴክኒክና ተራድኦ ድርጅት/ ጂቲዜድ/ ዓለም አቀፍ አገልግሎት አስታወቀ፡፡ በድርጅቱ የዩኒቨርስቲ አቅም ግንባታ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሚስተር ስቴፈን ሄልሚንግ እና የፕሮጀክት ክትትልና ትንተና ኃላፊ አቶ ቢኒያም መለኮት በአዳማ ዩኒቨርሲት ጉብኝት ላይ እንዳስታወቁት ድርጅቱ የዩኒቨርስቲዎች ግንባታ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርገው መንግስት በሰጠው ውክልና መሰረት ነው፡፡ ድርጅቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በገባው ውል መሠረት የ13 አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ግንባታና የሁለት ዮኒቨርስቲዎች ማስፋፊያ ሥራ ጥራትና ደረጃቸውን ጠብቀው በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ አምና በሁሉም ክልሎች በሚያዝያና ግንቦት ወራት በተጀመሩ በእነዚሁ ዩኒቨርስቲዎች ግንባታና ማስፋፊያ ሥራ 13 ከፍተኛ የሥራ ተቋራጮች በግንባታው በመሳተፋቸው ድርጅቱ ኃላፊነት ወስዶ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በበላይነት እየመራ መሆኑን ዳይሬክተሩና ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ ተከፍሎ በመካሄድ ላይ ካለው የዩኒቨርስቲዎች ግንባታ ሥራ አብዛኛው የተማሪዎች መማሪያ፣ መኝታ፣ ቤተመጽሓፍትና የመመገቢያ ክፍሎች በመጠናቀቅ ላይ በመሆናቸው አሥራ አንድ ዩኒቨርስቲዎች በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ8ሺ 800 በላይ ተማሪዎችን በመቀበል መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀመሩ አስረድተዋል፡፡ በአዳማ፣ አክሱም፣ ደብረ-ብርሃን፣ ደብረ-ማርቆስ ፣ ዲላ፣ ድሬደዋ፣ ጅጅጋ፣ ደሴና ኮምቦልቻ፣ ቴፒና ሚዛን ተፈሪ፣ ነቀምቴ፣ ሮቤ፣ ሰመራና ሶዶ ከተሞች በመካሄድ ላይ ባሉት ዩኒቨርስቲዎች ግንባታ 11ሺ ያህል ሥራ አጥ ዜጐች የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ በመላው አገሪቱ የዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ማካሄዱ በአገሪቱ ልማትን ለማፋጠን የሚያስችል የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ለትምህርቱ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ያሳያል ብለዋል፡፡ በአራት ምዕራፎች ተከፍሎ በመካሄድ ላይ ያለው የዩኒቨርስቲዎች ግንባታና ማስፋፊያ ሥራ ከ3 ዓመት በኋላ ሲጠናቀቅ በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ከ121 ሺ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መታቀዱን የሥራ ኃላፊዎቹ ገልፀው ድርጅቱም ለመንግስት ተገቢውን እገዛ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ አንዳንድ የአዳማና ነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የዩኒቨርስቲዎች ግንባታ በመጀመሩ በቀን ሥራ ተቀጥረው በወር ከ250 እስከ 300 ብር ገቢ በማግኘት ከሥራ አጥነት ችግር መላቀቅ እንደቻሉ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡ |
|
|
|
|