ኮሎኔል ናቃቸው ጫቅሌ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ተፈፀመ

ጎንደር ግንቦት 16/1998 /ዋኢማ/ለህዝቦች ነፃነት ሲሉ ለ31 ዓመታት አኩሪ ትግል ያካሄዱት የኮሎኔል ናቃቸው ጫቅሌ የቀብር ስነ- ስርዓት አቶ አዲሱ ለገሰን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፤ ዘመዶቻቸው እና የትግል ጓዶቻቸው በተገኙበት በጎንደር ከተማ በዛሬው ዕለት በታላቅ ክብር ተፈፀመ።

በመንበረ መንግስት መድሃኔዓለም ቤተ-ክርስቲያን በተካሄደው የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ በተነበበው የሕይወት ታሪካቸው ላይ ኮሎኔል ናቃቸው ጫቅሌ በሰሜን ጎንደር ዞን ከአባታቸው ከአቶ ጨቅሌ ሲሳይ ከእናታቸው ከወይዘሮ ውቢት የኔሁን በ1949 በታች አርማጭሆ ወረዳ ልዩ ስሙ ጭልቋና በተባለው መንደር ተወለዱ።

በአራት አበይት የትግል ሂደቶች ተከፍሎ በቀረበው የሕይወት ታሪካቸው ላይ እንደተመለከተው ኮሎኔል ናቃቸው ጫቅሌ የንጉሱን እና የደርግን አምባገነን ስርዓትን በመቃወም ከልጅነት ዕድሜአቸው ከ19 67 ዓ.ም ጀምሮ ታግለዋል።

የመጀመሪያው የኮለኔሉ የትግል ሂደት ኢዲዩ እና ኢህአፓ የታጋዩን የአርማጭሆን ህዝብ ትግል መምራት ተስኗቸው መፍረክረክ በጀመሩበት ጊዜ የአርማጭሆ አርበኞች ግንባርን በመምራት ተስፋ ከቆረጡት የተጠቀሱ ድረጅቶች እና አጋጣሚውን ተጠቅሞ ወደ አካባቢዉ በመግባት በህዝቡ ላይ ችግር ለመፍጠር አስቦ የነበረዉን ደርግን በቆራጥነት በመታገል ህዝቡን ታድገዋል።

በኋላም ወደ ኢህዴን ተቀላቅለው አምባገነኑን የደርግ ስርዓት በተለያዩ አዉደ ዉጊያዎች በቆራጥነት መታገላቸው ተገልጿል።

በሽግግሩ ወቅት በቴወድሮስ ክፍለ ጦር ምክትል ብርጌድ አዛዥ፤ከሽግግሩ ማብቂያ በኋላም የ31ኛ ክፍለ ጦር የ2ኛ ብርጌድ አዛዥ በመሆን ማገልገላቸው በሕይወት ታሪካቸዉ ላይ ተመልክቷል።

የሻቢያን ወራሪ ሀይል ለመመከት የምዕራብ ግንባር ተብሎ በሚጠራዉ በባድመ አካባቢ ተሰልፎ የነበረዉን የ31ኛ ክፍለ ጦር 2ኛ ብርጌድን መምራትን ጨምሮ በተለይ በዕርድ ማቴወስ እና በሌሎችም አዉደ-ዉጊያዎች ሃላፊነታቸውን መወጣታቸውንና ብቁ አመራር መስጠታቸው ተገልጿል።

ኮሎኔል ናቃቸዉ የኤርትራን ወራሪ ሀይል ምኞች በማክሸፍ ለሰጠት በሳል አመራር የ37ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ሆነዉ የተሾሙ ሲሆን እስከ ህይወታቸዉ ፍፃሜ ድረስም የ33ኛ የዓባይ ክፍለ ጦር አዛዥ በመሆን እንዳገለገሉ በህይወት ታሪካቸዉ ላይ ተመልክቷል።

በቀብር ስነ-ስርዓታቸው ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ፤የመከላከያ ሚኒስቴሩ አቶ ኩማ ደመቅሳ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ አያሌው ጎበዜን ጨምሮ ከፍተኛ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች፤የሰራዊቱ አባላት፤የትግል ጓዶቻቸው፤የትግል አጋሮቻቸው ፤የሰሜን ጎንደር ዞን ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።

ለ31 ዓመታትን አኩሪ የትግል ጉዞን ያሳለፉትና በተወለዱ በ49 ዓመታቸው በድንገተኛ ህመም በጦር ኃይሎች ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከትናንት በስቲያ ህይወታቸው ያለፈው ኮሎኔል ናቃቸው ባለትዳርና የ2 ሴቶችና የ4 ወንድ ልጆች አባት እንደነበሩ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።