|
የአመፅ ኃይሎች በመረጡትመንገድ እንዲቀጥሉ መፍቀድ የህግ የበላይነት እንዲጠፋ መፍረድመሆኑ ተገለጸ |
![]() አዲስ አበባ ግንቦት 16/1998/ዋኢማ/ ዓመፅን የመረጡ ኃይሎች በመረጡት የብጥብጥ መንገድ እንዲቀጥሉ መፍቀድ አገሪቱን ወደ ማያቋርጥ ትርምስና ግጭት ገብታ የህግ የበላይነት እንዲጠፋ መፍረድ ነው ሲሉ አቶ አባይ ፀሐዬ ገለፁ፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ አደረጃጀትና ተሳትፎ አማካሪ አቶ አባይ ፀሃዬ የግንቦት 20ን አስራ አምስተኛ ዓመት የድል በዓል ምክንያት በማድረግ ታትሞ ከወጣው አብዬታዊ ዴሞክራሲ መፅሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት አመፀኞችና ህገወጦችን እንደፈለጉ እንዲፈነጩ መፍቀድ የህግ የበላይነት፤ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲጠፋ መበየን ነው፡፡ ከግንቦት ምርጫ ወዲህ የአገራችን ዴሞክራሲ አደጋ ላይ ወድቋል ተብሎ በአንዳንድ ወገኖች የሚቀርበውን አስተያየት አስመልክተው አቶ አባይ እንደገለፁት፤ “ቅንጅትና የመሳሰሉት የዓመፅን መንገድ የመረጡ ኃይሎች አገሪቱን ወደ ማያቋርጥ ትርምስና ወደ ማያባራ ግጭት እንዲመሯት ስላልተፈቀደላቸው የዲሞክራሲ ጅምሩ ተቀልብሷል ማለት አይቻልም” ብልዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁከትና ግርግርን እርግፍ አድርገው በመተው በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ ባሉ ምክር ቤቶች ሃሳባቸውን እያራመዱ ባሉበትና አብዛኛው ህዝብ የአመፅ ኃይሎችን ባልመረጠበት ሁኔታ በአገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መኖሩን ያመለክታል እንጂ ወደ ኋላ መመለስን አያሳይም ብለዋል፡፡ የእስከአሁኑ የኢህአዴግ ትልቁ ችግር የኢህአዴግ ድርጅታዊ መሰረት ጠቦ መቆየቱ ነው ያሉት አቶ አባይ ይህንን ችግር ለመፍታትም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በስፋት የመመልመል ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተለይ መላላት ጀምሮ የነበረው የኢህአዴግና የአርሶ አደሩ ትስስር ለማጠናከር ድርጅቱ ጉድለቱን በማስተካከል መልካም አስተዳደርና ልማት የሚሰፍንበትን ሁኔታ በማመቻቸት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ወደ ድርጅቱ ተቀላቅለው የየአካባቢያቸውን የአስተዳደርና የድርጃቱን መዋቅሮች እንዲቆጣጠሩት መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ''ከምሁራንና ከወጣቶች እርቀን መቆየታችንና ለንግዱ ማህበረሰብ በአንዳንድ ጉዳዮች አግባብነት ያላቸው ስራዎች ሳንሰራለት መቆየታችን በከተማ የነበረን ተቀባይነት እንዳይሰፋ አድርጎት ቆይቷል'' ብለዋል፡፡ በዚህ መስክ ድርጅቱ የነበረበትን ችግር በስፋትና በጥልቀት በመገምገም የማስተካከያ እርምጃዎች በመውሰዱ በከተሞች የልማትና የመልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችል ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡ ከመምህራን ከወጣቶችና ከሴቶች ጋር ትስስሩን ለማጠናከርና በነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የድርጅቱን መዋቅር ለማስፋት የሚያስችለውን ሰፋፊ ስራዎች እየሰራ እንደሆነም አቶ አባይ ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ የወጣቶችን ፍላጎትና አመለካከቶችን ብዙም የተገነዘበ እንዳልነበር አቶ አባይ አመልክተው አብዛኛው ወጣት የኢህአዴግንም ሆነ የደርግን ባህሪያትና ታሪክ የማያውቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለተለያዩ የአስተሳሰብ ችግሮች ተጋልጦ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የምሁራንን አስተያየትና ፍላጎት ግምት ውስጥ ለማስገባት የተደረገው ጥረት ደካማ ስለነበር ምሁራን ወደ ድርጅቱ እንዳይጠጉና በአመለካከት ደረጃ ያሉ ልዩነቶች እንዲሰፉ አስተዋጽኦ ማድረጉን አቶ አባይ ጠቁመው፤ ድርጅቱ ከምርጫው በኋላ ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ መወያየት በመጀመሩ ስምምነትና መግባባት በተደረሰባቸው ጉዳዮች በጋራ ለመስራት የሚያስችል አመቺ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡ ባለሀብቱ ያለበትን የኢንቨስትመንት ማነቆዎች ለመፍታት በመሰረተ ልማት፤ በኤክስፖርትና በአሰራር የነበሩበትን ችግሮች ለማቃለል ረጅምና ብዙ ርቀት የተሄደ ቢሆንም በቂና አመርቂ ባለመሆኑ በአዲስ ቅኝትና አመለካከት ጥረቱ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ደካማ እንደነበረ ያስታወሱት አቶ አባይ አብዛኛው የአገሩንና የመንግስትን ሁኔታ በቅጡ የማያውቅ ጥቂቶች ደግሞ ስለ አገሪቱ መጥፎ ገፅታ የሚናገሩበትና ሌላውን ዓለም የሚያወናብዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በውጭ የሚኖሩ አንዳንድ ወገኖች በዓመፅና በህገ-ወጥ መንገድ ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም የፈለጉ ኃይሎችን መፈንጫ ሆነው መቆየታቸውን የተናገሩት አቶ አባይ “ይህንን ለማስተካከል አዳዲስ ዕቅዶች አደረጃጀቶችና አቅጣጫዎች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር የምንሸጋገርበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን” ብለዋል፡፡ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የድርጅቱ መዋቅሮች ህዝቡን ያለ ማዳመጥና ያለማማከር ችግርጎልቶ ይታይ እንደነበርና ይህንን ለማስተካከል በድርጅትም ሆነ በመንግስት የቀበሌ መዋቅሮች ስር ነቀል በሆነ መንገድ እንዲታረሙ የሚያስችል አዲስ አደረጃጀት መዘርጋቱንም አቶ አባይ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ኢህአዴግ በሚንቀሳቀስባቸው ክልሎች የቀበሌና የወረዳ አስተዳደሮች ተገምግመው በህዝቡ አመኔታ ያለገኙ አመራሮች ተወግደው በሌላ የተተኩ ሲሆን አዳዲስ አደረጃጀቶችና ተቋሞችም ተዘርግተዋል በማለት አቶ አባይ መናገራቸውን ጋዜጣውን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡ |
|
|
|
|