|
በደርግ ዘመን በርካታ ሰዎችን ከእስር ነጻ ያወጣው የአግአዚ ኦፕሬሽን እንቅስቃሴ በፊልም ሊቀረጽ ነው |
መቀሌ ሐምሌ 14/1998/ዋኢማ/ የትግራይን ህዝብ ታሪክ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የፊልምና ስነ ጽሁፍ ስራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ ተገለጸ። በደርግ ዘመን በርካታ ሰዎችን ከእስር ነጻ ያወጣው የአግአዚ ኦፕሬሽን እንቅስቃሴ በፊልም ሊቀረጽ ነው።
የክልሉ ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኪሮስ ቢተው የአግአዚ ኦፕሬሽን ፊልም አሰራርን አስመልክቶ ትናንት ለአንድ ቀን በመቀሌ ከተማ በተካሄደው ዓውደ ጥናት ላይ እንደተናገሩት፤ የትግራይ ህዝብ ታሪክ በስነ ጽሁፍና በፊልም በተደራጀ መንገድ ተጽፎና በፊልም ተቀርጾ ለትውልድ ሊተላለፍ ይገባል። የክልሉ መንግስት የህዝቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ጀግንነት ለመገለፅ በጋራና በተጠናል ለሚንቀሳቀሱ ባለሙያዎችና ተቋሞች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል። የአግአዚ ኦፕሬሽን ፊልም ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ተፈራ በበኩላቸው የትግራይን ህዝብ የትግል ታሪክ በፊልም ቀርፀው ለማቀረብ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልፀው፤ በኦፕሬሽኑ ተመስርቶ በሚሰራው ፊልም የህዝቡና የመሪ ድርጅቱ ህወሓት ግጭቶችን በብልሃት የመፍታት ጥበብ በስፋት እንደሚንፀባረቅ አስረድተዋል። የፊልሙ መሰረታዊ ሃሳብ ጥቂት ፈጠራ ታክሎበት የትግራይን ህዝብና መንግስት የልማት ስራዎች በማካተት በታማኝና ሃቀኛ ድርጊት ፍፃሚ መመስረቱን ገልጸው፤ ድርጅታቸው ለፊልሙ ቀረፃ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር መመደቡን ተናግረዋል። በዓውደ ጥናቱ የመገናኛ ብዙኋን ባለሙያዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና በአግአዚ ኦፕሬሽን ከእስር ቤት ነጻ የወጡ ሰዎች መሳተፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል። |
|
|
|
|