የአክራሪውና የሻዕቢያን ተልኮ ለማስፈፀም የተንቀሳቀሱ ቅጥረኞች ፀረ ህዝብ ሀይሎች ተደመሰሱ

ጅጅጋ ነሀሴ 3/1998/ ዋኢማ/የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስና አከባቢውን የአሸባሪዎች መነሃሪያ ለማድረግ ሶማሊያ ውስጥ የመሸገው አክራሪው ቡድንና ሻዕቢያ በሶማሊያ ክልል ያሰማራቸው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ቅጥረኞች መደምሰሳቸውን የሱማሌ ክልል የፀጥታና ፍትህ ማስተባበሪያ ጠቅላይ ቢሮ ገለፀ።

የማስተባበሪያው ምክትል ቢሮ ሀላፊ አብዲመሀመድ አረብ ዛሬ እንደገለፁት የሱማሌ ክልል ህዝብና መላ የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ ያቋቋሙትን አንድነት ለመናድና በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው ልማትና ዲሞክራሲ ለማደናቀፍ ሻዕቢያና ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እንደ አልኢትሀድ የመሳሰሉ አሸባሪ ሀይሎች ለተልዕኳቸው ማስፈጸሚያ የመረጡትን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ቅጥረኛ ድርጅት በማሰማራት በሱማሌ አንዳንድ አከባቢዎች የጀመሩት እንቅስቃሴ ከሽፏል ።

በአከራሪ ሀይሎቹና በሻዕቢያ የሚደገፈው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር /ኦ ኤን ኤል ኤፍ/ በክልሉ አንዳንድ ወረዳዎች የድርጅቱ ደጋፊዎች አይደሉም ያላቸውን ማሰር መግደልና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸም በመጀመሩ ይህ ጸረ ህዝብና ጸረ ሰላም ተግባሩን ማቆም አስፈላጊ እንደነበር ገልጸዋል።

ሶማሊያ ውስጥ በመሸገው አከራሪ ሀይል የሚሽከረከሩት እነዚህ ጸረ ሰላም ሃይሎች የሁሉም ሀይማኖቶች እኩልነት በህገመንግስት በተረጋገጠበት ሀገር እኛ ከምንለውና ከምናምንበት ውጭ ሌላ አማራጭ ሃሳብ አንቀበልም በማለት በአከባቢው ህዝብና መንግስት ላይ ጦርነት አውጀው ከሻዕቢያና ከአክራሪዎቹ ጋር ያላቸውን የዓላማ አንድነት ማረጋገጣቸውን ምክትል ሃላፊው አስረድተዋል።

እነዚሁ ኤርትራ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱና የትጥቅ ድጋፍ ተሰጥቷቸው ሶማለያን ተሻግረው ነፃ መሬትን በመጠቀም በቀብሪደሀር ፤ በጎዴ ፤ በአፍዴርኢሚ ፤ በፊቅና ደገሀቡር በአንዳነድ ቦታዎች ሰርገው በመግባት የሻዕቢያን ተልዕኮ ለማስፈፀም የጀመሩት የሽብር ድርጊት በአከባቢው ህዝብ ሙሉ ተሳትፎ መምከኑን ተናግረዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት፤የአከባቢው ሚሊሺያና ህዝቡ የጸረ ሰላም ሃይሎቹን ድርጊት ለመመከት በወሰዱት የተቀናጀ እርምጃ 13 የጸረ ሰላም ሃይሎቹ ከፍተኛ አመራር አባላትና የጦር መሪዎችን ጨምሮ በርካታ የጸረ ሰላም ሃይሎቹ ቅጥረኞች መደምሰሳቸውንና ከፊሎቹ ደግሞ መማረካቸውን አስረድተዋል።

እነዚሁ ከተራ ሽፍትነት ባልተለየ የአካባቢውን ሰላም በማደፍረስ ተግባር ላይ ተሰማርተው የቆዩትና በተወሰደው እርምጃ ከተደመሰሱት መሀከል በጎዴ ፤ ቀብሪደሀሪና አፍዴር በመንቀሳቀስ የሽብርና የዘረፋ ተግባር ሲመሩና ሲያስተባብሩ የነበሩት በቅፅል ስማቸው ደቡኬ እና ዊልዋል የተባሉት ቀንደኛ መሪዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

አካባቢውን ከጸረ ሰላም ሃይሎቹ ለመጠበቅ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት የክልሉ የፀጥታና ፍትህ ማስተባበሪያ ምክትል ቢሮ ሀላፊው ህዝቡም የአካባቢውን ፀጥታ በመጠበቅ በኩል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የአከባቢው የጸጥታ ሃይሎች፤ የአገር መከላከያ ሰራዊት ህዝቡን በማሳተፍ የአከባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንደተጠናቀቀ ለህዝቡ ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።